እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ በሰላም አሸጋገርዎ!!
ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን #Tekleye24
መርሃ ግብሮቻችንን ለመከታተል ይረዳዎት ዘንድ www.facebook.com/Tekleye24 ይጫኑ ፡፡
የተክለ ሃይማኖት ማኅሌትና ዝማሬ (ግንቦት ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም)
ኪዳነ ምሕረት
በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ
ኪዳን የሚለው ቃል "ቃል" ከሚለው ጋር እየተዛረፈ በብሉይ ኪዳን ለ280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲሰ ኪዳን ደግሞ ከ32 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ "ኪዳን" ቃሉ "ተካየደ" ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ "ምሕረት" የሚለው ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡
"ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አድርጋለሁ" ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ ወደፊትም ያደርጋል፡፡ (መዝ88.3) ቃል ኪዳኑም የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡
በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት እናቶች ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸውና የምሕረት ቃል ኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዙሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ከትቦ ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡትና አፈርና ለተጋደሉበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡
መላእክትን "ያድናሉ" ማለት ስሕተት ነውን?
በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ
ለመሆኑ መላእክት ማዳን ይችላሉ ማለት ስሕተት ነውን? ዛሬ ዛሬ ብዙዎች መናፍቃን መላእክትን "ያድናሉ" ማለት እንደ ስሕተትና እንደ ክህደት ቆጥረውት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለምን ሲባሉም መጽሐፍ ቅዱስ "መዳን በሌላ በማንም የለም" በማለት ያለ አገባቡ ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡፡
በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መላእክት አያድኑም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ዕድሜ ይስጠን እንጂ ራሱን በቻለ ርእስ በሌላ ጊዜ በሰፊው እንመለስበታለን፡፡ ለዛሬ የመላእክትን ማዳን ከመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ እየጠቀስን እንመልከት፡፡
ቅዱስ ዳዊት በግልጥ "የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል" ይላል፡፡ (መዝ33.7) ጥቅሱ "ያድናቸውማል" ማለቱን ልብ በሉ፡፡ መላእክት የማያድኑ ቢሆኑ ኖሮ ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ ግልጥ አድርጎ "ያድናቸውማል" ይል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ከመሰከረው እውነት የሚበልጥ ዕውቀት አለንን? እርሱ "ያድናሉ" እያለ እኛ "አያድኑም" ብንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ጥቅስ ውሸት ነውን? ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንታዘዘዋለን? እናምነዋለን? ወይስ ልናርመው እንወዳለን?