ስለ ሃገረ ስብከታችን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ እንቅስቃሴ የጀመረችው ከስድሳ ዓመታት በፊት በ፲፱፻፴፯ ዓም እ.ኤ.አ. አካባቢ ነው። በዚያ ወቅት ወርልድ ፌዴሬሽን የተባለው እና ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ድጋፍ ለማሰባሰብ በእነ መላኩ በያን አማካኝነት የተቋቋመ ድርጅት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለምዕራቡ ዓለም ከማስተዋወቁም በላይ በአሜሪካ እንዴት መቋቋም እንዳለባት ያለውን እቅድ ለመንበረ ፓትሪያሪኩ ልኮ ነበር።
ይህንን መሠረት በማድረግ አባ ገብረ ኢየሱስ መሸሻ (በኃላ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ) እና አቶ አበራ ጀምበሬ እ.ኤ.አ. በ፲፱፻፶፪ ዓም ለቤተ ክርስቲያን መተከል የሚያስፈልጉትን ንዋያተ ቅድሳት በማምጣት ጥናቱን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሱ። ከሁለት ዓመት በኃላም የሐረር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ አሜሪካ በመጡበት ጊዜ በአሜሪካ እና በካሪቢያን ደሴቶች ቤተ ክርስቲያንን ለመትከል ቅዱስ ሲኖዶስ ያሰበበት መሆኑን እና ይህም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተለጡ። በተገባውም ቃል መሠረት እ.ኤ.አ. ጥቅምት ፳፭ ቀን ፲፱፻፭፱ ዓም ተመልሰው ወደ ሰሜን አሜሪካ በመምጣት ዛሬ የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና በመሆን የሚያገለግለውን የቅስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት አከበሩ።
ቤተክርስቲያናችን በምዕራቡ ዓለም ሀገረ ስብከት ያቋቋመችው በ፲፱፻፬፭ ዓም ሲሆን ሀገረ ስብከቱም “የምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ሀገረ ስብከት” የሚባል ሲሆን ከእንግሊዝ በመለስ ያሉትን አፍሪካን ጨምሮ በሙሉ ያጠቃልል ነበር። ይህም ለሃምሳ ዓመታት ያህል በዚሁ ሁኔታ ቆይቷል። በቦታውም በመጀመሪያ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ በኃላም ብፁዕ አቡነ ኢስሐቅ ተሾመው አገልግለውበታል።
ቤተክርስቲያናችን በምዕራቡ ዓለም ሀገረ ስብከት ያቋቋመችው በ፲፱፻፬፭ ዓም ሲሆን ሀገረ ስብከቱም “የምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ሀገረ ስብከት” የሚባል ሲሆን ከእንግሊዝ በመለስ ያሉትን አፍሪካን ጨምሮ በሙሉ ያጠቃልል ነበር። ይህም ለሃምሳ ዓመታት ያህል በዚሁ ሁኔታ ቆይቷል። በቦታውም በመጀመሪያ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ፣ በኃላም ብፁዕ አቡነ ኢስሐቅ ተሾመው አገልግለውበታል።
በ፲፱፻፺፪ እ.ኤ.አ. ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት የምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ሀገረ ስብከት ለአራት ተከፈለ። ምሥራቅ አፍሪቃ፣ አውሮፓ፣ ካናዳ፣ የተባበሩት አሜሪካ እና ካናዳ እንዲሁም የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ደሴቶች። እ.ኤ.አ. በ፲፱፻፺፭ ዓም ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና ካናዳ ሁለት አህጉረ ስብከት ሆነ። በዚህ ዘመንም ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለብዙ ዘመናት አገልግለውበታል። በ፲፱፻፺፰ ዓም ደግሞ የተባበሩት አሜሪካ ወደ ሦስት አህጉረ ስብከት ተከፈለ። ካሊፎርኒያ እና ምዕራብ አሜሪካ፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው፣ እንዲሁም ኒውዮርክ እና አካባቢው።
የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ታሪክ እና የሥራ እንቅስቃሴ
የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተመሠረተው በ፲፱፻፺፰ ዓም ነው። በወቅቱ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ለኒውዮርክ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ለካሊፎርኒያ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ለዋሽንግተን ዲሲ ተመደቡ። ነገር ግን ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ብዙም ሳይቆዩ ተዛወሩ። በምትካቸው ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ለዋሽንግተን ሀገረ ስብከት ተሰየሙ።
ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አብያተ ክርስቲያናትን ለማቀራረብ፣ ከእናት ቤተክርስቲን መዋቅር የወጡትን ወደ መዋቅሩ ለማስገባት፣ ምእመናንንም ከእናት ቤተ ክርስቲያን ማዋቅር ጋር ለማስተዋወቅ በአያሌ ደክመዋል። በተለያዩ አጥቢያዎች እና ጉባኤያት ላይ በመገኘት በዕንባ ጭምር ችግሮችን ለመፍታት ተጋድለዋል።
ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በ፳፻ ዓም ሲዛወሩ ሀገረ ስብከቱን ብፁዕ አቡነ አብርሃም ደርበው እንዲያስተዳድሩት ተደረገ። ብፁዕ አቡነ አብርሃም ከካህናት እና ከአባቶች ጋር በመወያየት፣ ወጣቶችን አቅርበው በማነጋገር፣ ለሕዝቡ ጥያቄዎችን ግልጽ መልስ በመስጠት የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከትን በማጠናከር ሥራ ጀመሩ።
በተለይም በሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ፣ በማኅበረ በዓለ ወልድ ጉባኤ እና በማኅበረ ቅዱሳን ጉባኤያት እየተገኙ የሀገረ ስብከትን ጥቅም፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ያለውን አስተዋጽዖ እና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንፃር ያለውን ሁኔታ አስረዱ።
በዚህም መሠረት የዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስንከትን ለማጠናከር ዕቅድ ተነደፈ።
- ፩. ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተሾመው ሲመጡ በማረፊያ እጥረት ስለሚንገላቱ ራሱን የቻለ መንበረ ጵጵስና እንዲኖረው
- ፪. ሀገረ ስብከቱ በአሜሪካ ሕግ እንዲመዘገብ
- ፫. ጽሕፈት ቤት እና መንበረ ጵጵስና አጥቢያ እንዲኖረው
- ፬. ከአካባቢው አገልጋዮች ጋር ውይይት እንዲደረግ
በዕቅዱም መሠረት ችግሮችን ለመፍታት በቆረጡ ካህናት፣ አባቶች፣ እናቶች ወንድሞች እና እኅቶች አማካኝነት መሰባሰብ እና መወያየት ተጀመረ። ብፁዕ አቡነ አብርሃም ከካህናቱ እና ከወጣቶቹ ጋር ባደረጉት ተደጋጋሚ ውይይት በተኘው ግንዛቤ መሠረት ሀገረ ስብከቱን የሚያደራጅ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቋመ።
የኮሚቴው የመጀመሪያ ሥራ ሀገረ ስብከቱን በአሜሪካ ሕግ መሠረት ማስመዝገብ ሲሆን ይኼውም ተጠናቀቀ። በመቀጠልም ልዩ ልዩ ጉባኤያትን በማድረግ፣ ድረ ገጽ በመክፈት እና የውይይት መርኃግብር በመዘርጋት ሀገረ ስብከቱን ለማስተዋወቅ ተሞከረ።
ሀገረ ስብከቱን የማቋቋሙ ሥራ የሁሉም ካህናት እና ምዕመናን ግዴታ በመሆኑ በአካባቢው ከሚገኙ ሁሉም ዓይነት ካህናት እና የቤተ ክርስቲያን አመራር አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ በየጊዜው ተሞክሯል። ነገር ግን በወጣቶቹ በኩል የታየውን ያህል ፈቃደኝነት በአንዳንዶቹ ዘንድ ሊገኝ አልቻለም።
መንበረ ጵጵስናውን ለማደራጀት በተደረገው ጥረት በብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥረት እና በምዕማናን የገንዘብ ርዳታ በአሌክሳንደሪያ ቨርጂኒያ የሚገኘውን ቤት ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፩ ዓም በመግዛት መንበረ ጵጵስናው ተቋቋመ።
የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት በብፁዕ አቡነ አብርሃም መሪነት ባለፉት ሦስት ዓመታት አያሌ ሥራዎችን አከናውኗል።
- በአሜሪካን ሀገር አገልግሎት የሚሰጡትን ሦስቱን ዓበይት ማኅበራት በማጠናከር በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር ያልነበሩትን ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር እንዲገቡ ከሌሎች አህጉረ ስብከት ጋር ሠርተዋል።
- በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ወደ አሥራ ስድስት አሳድጓል
- ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በሚመለከት ለሚነሡ ክርክሮች መፍትሔ ሰጥቷል
- የሀገረ ስብከቱን እንቅስቃሴ በመንበረ ፓትሪያሪክ የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አቅርቧል
- የሦስቱንም አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት እና ሥራ አስኪያጆችን በመጋበዝ በአሜሪካ ስላለው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውይይት እንዲካሄድ አድርጓል
- ወደ አሜሪካ ለተልዕኮ ለሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት አባታዊ ክብር በተሞላበት ሁናቴ አቀባበል፣ መስተንግዶ፣ እና አሸኛኘት አድርጓል
- የ፳፻፬ ዓም የመስቀል ደመራ በዓል በሀገረ ስብከት ደረጃ እንዲከበር አድርጓል
- የመንበረ ጵጵስና አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ አድርጓል
- የሀገረ ስብከቱን እንቅስቃሴ የሚገልጥ ድረ ገጽ አዘጋጅቷል
- ከ፲፪ በላይ ታላላቅ ጉባኤያትን አዘጋጅቷል
በአጠቃላይ ሀገረ ስብከቱ ያሉትን ፈተናዎች እና ጫናዎች በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ተቋቁሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልዕኮ ለማሳካት በመሥራት ላይ ይገኛል። እስከ አሁን የተከናወኑት የሥራው ጅማሬዎች እንጂ መጨረሻዎች አይደሉም። ወደፊትም ይበልጥ ተጠናክሮ እና ተደራጅቶ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት እና ለምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት መጠናከር በቃለ ዐዋዲው በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
በዚህ ጊዜ በተከታታይ ለሦስት ዓመታት ያለመታከት ቀን ከሌሊት ሲያገለግሉን የነበሩትን ብፁዕ አቡነ አብርሃም ለተመሳሳይ ሐዋሪያዊ ተልዕኮ ወደ ቅድስት ሀገረ ምስራቅ ሐረርጌ እና ጅጅጋ ስለሚሄዱ እኛም የአበውን ፈለግ ተከትለን የብፁዕነታቸውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የተክለሃይማኖት አምላክ ይርዳን፣ ለብፁዕነታቸውም በሄዱበት ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን አደራ በቅድስና እንዲወጡ እየተመኘን ረዥም እድሜን እና የአገልግሎት ዘመን እንመኝልዎታለን።