የምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ሠንበት ትምህርት ቤት አመሰራረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
የምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለሃይማኖት ሠንበት ትምሕህርት ቤ/ት በእግዚአብሄር ፈቃድና በብፁዕ አቡነ አብርሃም ሠብሳቢነት በጥቂት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ተመስርቷል ። ለዚህ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያዎቹ የሠንበት ትምህርት ቤቱ አባላት በተለይ በተለያዩ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ካሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሠንበት ትምህርት ቤት መጥትው የተሰባሰቡ በመሆናቸው በፊትም በሠንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት የሚታወቁ ስለነበረ ለመሰባሰብና ለመነጋገር ስለ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ቀናዒ ስለነበሩ እና ለመስራትና በተለይም በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ዓርአያ የሚሆን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚጓዝ ሠንበት ትምህርት ቤት ለመመስረት ብዙ ውጣ ውረድ ነበረበት።
ለሠንበት ትምህርት ቤቱ አገልግሎትና አባላቱን ለማሰባሰብ ትልቅ ፈተና የነበረው የትምህርት መማርያና የሠንበት ትምህርት ቤትን ጉባኤና መርሃ ግብሩን ማከናወኛ ቦታ ያለመኖር ነበር ። በወቅቱ በብፁዕ አቡነ አብርሃም ጠቋሚነት የሠንበት ትምህርት ቤቱን በቋሚነት ለማቋቋም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሲፋጠኑ በሚያዩዋቸው አገልጋዮች አማካኝነት የሠንበት ትምህርት ቤቱ የመጀመርያው ሥራ አመራር ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቀረ ። በወቅቱ የተመረጡት ሥራ አመራሮች ትልቁ ጭንቀትና የዘወትር ውይይታቸው የነበረው እንዴት ዓርአያ የሚሆኑ ወጣቶች በሠንበት ትምህርት ቤት እናዋቅርና እንቅረፅ ፣ አባላትስ እንዴት እናሰባስብ ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱም በኪራይ ስለነበረች ትምህርት እንዴት እና የት ይሰጥ ፣ መዝሙርስ የት ይጠና ፣ ለሠንበት ትምህርት ቤቱስ አገልግሎት የሚውሉ አልባሳትና ቁሳቁሶች እንዴት እናግኝና እናሟላ ነበር ። በወቅቱ በቦታ ማጣት ምክንያት ለእሁድ አገልግሎት የሚሆን መዝሙር የሚጠናው በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተከራይታ ትጠቀምበት የነበረው የሌላ እምነት ተከታዮች ስለነበረ እነሱ ለአገልግሎት ይጠቀሙበት በነበረ “ፒያኖ“ ዙሪያ ፒያኖውን እንደ ጠረጴዛ በመጠቀም መዝሙር ያጠኑ ነበረ ። እንደውም ከመስራቾቹ አንድ ወንድም ወደፊት ይቺን ፒያኖ በትዝታ የምናስብበት ጊዜ ይመጣል ብሎ አባላቱን ፈገግ አሰኝቷል ።
ቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያየ ቦታ በኪራይ ምክንያት ብትቀያይርም ሁሉም የሠንበት ትምህርት ቤቱ አባላት በዓላማ የተሰባሰቡ በመሆናቸው ፀንተው በመግፋት አሁን ላለብት ደረጃ ትልቅ ተጋድሎ አድርገዋል። ሠንበት ትምህርት ቤቱም ከምስረታው ጀምሮ እስከ አሁን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በጠበቀና “ ቃለ አዋዲውን “ በተከተለ መልኩ መተዳደርያ ደንብ በመቅረፅ ከቤተ ክርስቲያኒቱ “ ሠበካ ጉባኤ “ ስር በመሆንና መመርያ በመቀበል የእናት ቤተ ክርስቲያን ድምጽ በመስማት አገልግሎቱን በማካሄድ ላይ ይገኛል ። ሠንበት ትምህርት ቤቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ትጋቱና ዕድገቱ በፈቃደ እግዚአብሔር እየጨመረ መጥቷል ።
ለዚህም በብፁዕ አቡነ አብርሃም ጠያቂነት አስራ ሁለተኛውን የሰሜን አሜሪካ የሠንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት ችሏል። ሠንበት ትምህርት ቤቱም በቃለ አዋዲው መሰረት በየሦስት ዓመቱ የሚቀየር የሥራ አመራር እየመረጠ አገልግሎቱን እያካሄደ ይገኛል ። የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን መደበኛ መርኃግብር ዘርግቶ በአሁኑ ሰዓት ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ከነዚህም በከፊል:
- በተቻለ አቅም ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደርና ከሰበካ ጉባኤው ጋር ቋሚ የሆነ በየወሩና በየሁለት ወሩ የጋራ ስብሰባ በማድረግ ለወደፊቱ የቤተ ክርስቲያን እድገት አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል ።
- የምሥራቀ ፀሐይ ሠንበት ትምህርት ቤት ሣምንታዊና ተከታታይ የሆነ ለአባላቱ ኮርስ (ትምህርት) በካህናት አባቶችና ዲያቆናት አማካኝነት እየተስጠ ይገኛል።
- የሰብበት ትምህርት ቤታችንን በፈቃደ በእግዚአብሄርና በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በኢትዮጵያዊው ጻድቅ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ረዳትና ምልጃ በቅርቡ ሥራዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ የአባቶችን ፈለግ የተከተለ ያሬዳዊ ዜማ የምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሠንበት ትምሕህርት ቤት “ዘማዕት ዘኢትዮጵያ” ቁጥር አንድ መዝሙር በመስራት ላይ ሲሆን በቅርቡ ለህትመት ይበቃል ።
ይህንን ሁሉ ላደረገ ለቅዱሳን አምላክ እግዚአበሄር ዘወትር ክብር ምስጋና ይግባው ። በእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እና በምልጃቸው ላልተለዩን ለጻድቁ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ክብርና ምስጋና እናቀርባለን።
ማሳሰቢያ
ከላይ ከተነለፁት መንፈሳዊ ተግባራት በተጨማሪ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ለሽያጭ የምናቀርባቸውና በትእዛዝ የምንሰራቸው ንዋያተ ቅድሳት ለመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በትዕዛዝ እናደርሳለን ከነዚህም ጥቂቶቹ:
- ጧፍ
- ዣንጥላ
- የፀሎት መፃህፍትና ለመንፈሳዊ እውቀት የሚረዱ የቤተክርስቲያን መፃህፍትን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳትን እናቀርባለን
ለተጨማሪ ማብራሪያና የትእዛዝ ጥያቄዎ በሚከተሉት የስልክ ቁጥሮች ያግኙን 202-528-4802 ወይም 703-386-6730
የጻድቁ አባታችን አማላጅነት እና ረደኤት አይለየን........ አሜን!!!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ሃገረ ስብከት ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ተክለሃይማኖት ሰብበት ትምሕርት ቤት